ጥሩ ፍቅር እንዳይኖረን የሚያደርጉ ነገሮች

ጥሩ የፍቅር ህይወት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ተግባራት አሉ። መፅሐፍ “ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳል” እንዲል መልካም ተግባር መልካም የፍቅር ውጤትን ሲያስገኝ ጥሩ ያልሆነ ተግባር ለመለያየትና ለጭቅጭቅ ይዳርጋል።ጥሩ ፍቅር እንዳይኖረን የሚያደርጉንን ተግባራት በማወቅ የፍቅር ህይወታችንን ማስተካከል እንችላለን። ከነዚህም ዋነኞቹ የምላቸው ፦


1. ከሌላ መጠበቅ (Expectation)

አንዳንድ ሰው ከሌላ የሚደረግን ነገር የመጠበቅ አባዜ አለበት። ለነገሩ ምን አደረገልሽ ብሎ የሚጠይቅ ይበዛል እንጂ ምን አደረግሽለት የሚልሽ ጥቂት ነው።


እሱ እንዲያደርግልሽ የምትፈልጊውን ያን ደግሞ አድርጊለት፤ የምትጠብቂውን የፍቅር ቃላትና ተግባር ለምን አንቺ አታደርጊለትም?።


ከሷ የምትጠብቀውን ታማኝነት አንተ ተግብረው። ከሌላው የምንጠብቀውን ነገር ራሳችን የምናከናውነው ቢሆን በፍቅራችን ችግር ይኖር ነበር?። የሌላውን ከመፈለጋችን በፊት የራሳችንን እንወጣ።2. አጉል ፉክክር (Competition)

ፉክክር ያለው ህጻናት ጋር ብቻ ነው ካላችሁ ዞር ዞር ብላችሁ አከባብያችሁን እዩት አንዳንድ ጥንዶች ከህፃን የባሰ ነውኮ ፉክክራቸው። ያ ፉክክር መበቀልንም ሊጨምር ይችላል። የፊክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንዲሉ በአጉል ፉክክር ምክንያት ፍቅራቸውን ሳያጣጥሙ እንዲሁ እንደባዘኑ ይቆያሉ።3. ቅናትና የከፋ ጥርጣሬ (Jealousy)

የፍቅር ህይወት ውስጥ የከፋ ጥርጣሬ በጣም መርዝ ነው። ኦኦኦ ስልክሽን ቶሎ ካልመለሰ በቃ እንደለመደው ከዛች ጋር ተጋድሞልኝ ይሆናል፣ ከስራ አርፍዳ ከገባች ከአለቃዋ ጋር ተጋድማ ይሆናል፣ አቤት ጉድ የጥርጣሬ ብዛት ማቆምያ የለውም። በርግጥ ጥርጣሬ ባብዛኛው ካለመተማመን የሚመነጭ ነው።4. መውቀስ / ወቀሳ (Blaming)

ከሰው መካከል የሚገኝን ስህተት እንደመለየት የሚቀል ነገር ያለ አይመስለኝም። እንዲህ ሆንሽ እንዲህ ሆንክ መውቀስ የፍቅር ነቀዝ ነው። በርግጥ ሰው ደካማ ነውና ማጥፋቱ ስለማይቀር መወቀሱ አይቀርም። የብዙ ሰው ወቀሳ ግን የራስን የበላይነት ለማሳየት ነው።


ልክ እንደ ፖለቲካ ፖርቲዎች ዝም ብሎ መውቀስ ምክንያቱ ደግሞ ሌላውን ጥሎ ለራስ ለመንገስ ነው። ፍቅር እንዲህ ከሆነ ከባድ ነው።


"አቤት የሐበሻ ወንድ ፍቅር ያውቃል'ንዴ ደሞ ውይ ይፍጃቸው" ስላልሽ ፍቅረኛሽን አትቀይሪውም የሱን ክፋትም ለሌላ ስላወራሽ ስለወቀስሽውም ለውጥ አታመጪም። ከፍቅረኛሽ ጋር ፊት ለፊት ተቀመጪ ተወቃቀሺ ተወቃቀሱ


5. ስህተትን አለማመን / አለመቀበል

"ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም::" ፍጹም አይደለንም እንሳሳታለን የሰራነውን ስህተት ካላመንን ፍቅራችን እንዴት ወደፊት ሊራመድ ይችላል? ።


ስህተትን ከመቀበል ይልቅ ሞት የሚመርጥ አለ:: ስንቱ እንዲው ሲጀነን ትዳሩን በትኖ ልጆችን የሁለት ቤት ልጅ አደረገ። ቆም እንበል ወደ መሬት እንውረድ ስህተታችንን እንቀበል። ፍቅራችንን አሪፍ እናድርግ ከመበተን እንታደግ


ከላይ የጠቀስኳቸውን 5 ነገሮች ባለማድረግ ፍቅራችሁን ማጠንከር ትችላላችሁ። አሪፍ የሆነ ፍቅር ይዘዝባችሁ ይዘዝብን::


#አሽሩካ ነኝ

የይቅርታ ልብ ለሁላችን!

154 views0 comments